ፋውንዴሽናችን መጋቢት 11, 2014 ዓ.ም አመታዊ የዳውን ሲንድረም ቀንን “አካታችነት ማለት” በሚል መሪ ቃል በእግር ጉዞ እና በህፃናት ፌስቲቫል አክብሮ ውሏል። “መጋቢትን ከዲቦራ ጋር” በሚል ዝግጅት ሲከበር የዚህ አመት ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን “አካታችነት መብት እንጂ ችሮታ አይደለም” በማለት ከአእምሮ እድገት ጋር ከተወለዱ ህፃናት፣ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ቀኑ በድምቀት ተከብሯል።

በእለቱ በክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ የመክፈቻ ንግግር ፕሮግራሙ የተከፈተ ሲሆን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ስለ አአምሮ እድገት ውስንነት በተለይም ስለ ዳውን ሲንድረም ምንነት እና እነዚህን ህፃናት እንዴት የማህበረሰቡ አንድ አካል ማድረግ እንዳለበን መልእክት አስተላልፈዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ክብርት ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ የሰራተኛ እና ሴቶች ማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ እንዲሁም አቶ ኤፍሬም ተሰማ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ በበአሉ ላይ በመገኘት ለታዳሚዎች ንግግር አድርገዋል።

ህፃናቱ በተለያዩ ፕሮግራሞች እና ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ አስደሳች ቀንን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያሳለፉ ሲሆን በመጨረሻም ለፕሮግራሙ መሳካት የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት የእውቅና ሰርተፍኬት ከፋውንዴሽኑ ተበርክቶላቸዋል።